Ezekiel 15

የማይረባው የወይን ግንድ

1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ የወይን ግንድ በዱር ካሉት ዛፎች ሁሉ ቅርንጫፍ የሚሻለው በምንድን ነው? 3የሚጠቅም ነገር ለመሥራት ከግንዱ አንዳች ተወስዶ ያውቃልን? ዕቃ የሚንጠለጠልበትስ ኵላብ ከእርሱ ይበጃልን? 4እንዲነድድ እሳት ላይ ከተጣለ በኋላ፣ እሳቱ ጫፍና ጫፉን አቃጥሎ፣ መኻሉን ከለበለበው፣ ለአንዳች ነገር ይጠቅማልን? 5እንግዲህ ደኅና ሆኖ ሳለ ለምንም ነገር ካልጠቀመ፣ እሳት ካቃጠለውና ከለበለበው በኋላ ረብ የለሽነቱ የቱን ያህል የባሰ ይሆን!

6“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከዱር ዛፎች መካከል የወይን ግንድ እንዲነድድ ለእሳት አሳልፌ እንደ ሰጠሁ፣ እንዲሁ የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች አሳልፌ እሰጣለሁ። 7ፊቴን በክፋት ወደ እነርሱ እመልሳለሁ፤ ከእሳት ቢያመልጡም፣ ገና እሳት ይበላቸዋል። ፊቴን በክፋት ወደ እነርሱ በመለስሁ ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 8ታማኝ ካለመሆናችሁ የተነሣ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

Copyright information for AmhNASV